ስለ ባለስልጣኑ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተቋቋመ የፌዴራል መ/ቤት ሲሆን ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ባለሥልጣኑ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት መገናኛ ብዙኃንና የማስታወቂያ ዘርፍን በአጠቃላይ እንዲከታተል እና እንዲደግፍ ሆኖ ተቋቁሟል።
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት የባለሥልጣኑ ዓላማ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ መንግሥትና በኢትዮጵያ ላይ ግዴታ በሚጥሉ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን ሀሳብ በነፃነት የመግለፅና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕጉ መሠረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤ የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥርና ግምገማ እንዲጠናከር ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፤ በብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጥት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚነት፣ ባለቤትነት፣ዝግጅትና ሥርጭት ላይ ብዝኃነት እንዲጠበቅና እንዲስፋፋ መሥራት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ባለድረሻ አካላት በመደበኛነት የሚወያዩበት መድረክ ማመቻቸት፣በመገናኛ ብዙኃንና በመንግሥት አካላት መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት እንዲኖርና እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ባለሥልጣኑ የብሮድካስት፣ የህትመት እና የበየነመረብ መገናኛ ብዙኃንን ይመዘግባል፣ ፍቃድ ይሰጣል እንዲሁም የክትትል ስራ ይሰራል። በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ እና የማስታወቂያ አዋጅን ያስፈፅማል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንን ከመቆጣጠር ባለፈ የዘርፉን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግ እና የይዘት ብዝኃነት እንዲኖር በዘርፉ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራ ይሰራል፣ የሚዲያ ፖሊሲ መነሻ ሃሳቦችን ያመነጫል፡፡
Asset Publisher
ባለሥልጣኑ በቴከኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርዓትን ከመዘርጋት እና ከሰው ሃብት ስምሪት አንፃር የሰራቸው ስራዎች ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቆመ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባደረገው ምልከታ ባለሥልጣኑ በቴከኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርዓትን ከመዘርጋት እንዲሁም ከሰው ሃብት ስምሪት አንፃር የሰራቸው ስራዎች ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በባለሥልጣኑ በመገኘት የተለያዩ የስራ ክፍሎችን የጎበኘ ሲሆን በምልከታው ባለሥልጣኑ ከአሰራር ስርዓት ዝርጋታ፣በቴክኖሎጅ በመታገዘ ስራን ከማቀላጠፍ አንፃር እንዲሁም ከሰው ሃይል ስምሪት አንፃር ያመጣው ለውጥ አበረታች እና ተሞክሮ ሊሆን የሚችል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ ባለሥልጣኑ የሚያከናውናቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች፣ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት እንዲሁም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት በቴከኖሎጂ የታገዘ እና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች እየተከናወነ ያለ መሆኑ ሊበረታታና ሊቀጥል የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በጥራትና በቴክኒሎጂ በታገዘ መልኩ በመስራት የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ ለማሳካት የጀመራቸው ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉና ለሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ ሊሆኑ የሚገባቸው መሆናቸውንም ሰብሳቢው ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው የባለሥልጣኑን የስራ እንቅስቃሴ በመጎብኘቱ አመስግነው የአቅም ግምባታ ስራን እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አሰራርን በማዘመን ረገድ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃርም ከግንዛቤ ፈጠራ ስራ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡