ስለ ባለስልጣኑ

                የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተቋቋመ የፌዴራል /ቤት ሲሆን ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ባለሥልጣኑ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት መገናኛ ብዙኃንና የማስታወቂያ ዘርፍን በአጠቃላይ እንዲከታተል እና እንዲደግፍ ሆኖ ተቋቁሟል።

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት የባለሥልጣኑ ዓላማ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ መንግሥትና በኢትዮጵያ ላይ ግዴታ በሚጥሉ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን ሀሳብ በነፃነት የመግለፅና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕጉ መሠረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤ የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥርና ግምገማ እንዲጠናከር ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፤ በብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጥት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚነት፣ ባለቤትነት፣ዝግጅትና ሥርጭት ላይ ብዝኃነት እንዲጠበቅና እንዲስፋፋ መሥራት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ባለድረሻ አካላት በመደበኛነት የሚወያዩበት መድረክ ማመቻቸት፣በመገናኛ ብዙኃንና በመንግሥት አካላት መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት እንዲኖርና እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ባለሥልጣኑ የብሮድካስት፣ የህትመት እና የበየነመረብ መገናኛ ብዙኃንን ይመዘግባል፣ ፍቃድ ይሰጣል እንዲሁም የክትትል ስራ ይሰራል። በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ እና የማስታወቂያ አዋጅን ያስፈፅማል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንን ከመቆጣጠር ባለፈ የዘርፉን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግ እና የይዘት ብዝኃነት እንዲኖር በዘርፉ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራ ይሰራል፣ የሚዲያ ፖሊሲ መነሻ ሃሳቦችን ያመነጫል፡፡